የኮቪድ-19 ቀውስ በኢትዮጵያ የሚያስከትለውን የፖለቲካ አስተሳሰብ አያያዝ
የኮቪድ-19 ቀውስ በኢትዮጵያ የሚያስከትለውን የፖለቲካ አስተሳሰብ አያያዝ
Ethiopian election authority head Birtukan Mideksa (R) swears in during the handover ceremony at the Parliament in Addis Ababa, Ethiopia on 22 November 2018. Anadolu Agency/Minasse Wondimu Hailu via AFP

የኮቪድ-19 ቀውስ በኢትዮጵያ የሚያስከትለውን የፖለቲካ አስተሳሰብ አያያዝ

ኢትዮጵያ በኮቪድ-19 በሽታ ወረርሽኝ ምክንያት ለነሐሴ ታቅዶ የነበረውን ምርጫ ላልተወሰነ ጊዜ አስተላልፋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች። ሃገሪቱ ወደ መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ እየተንገዳገደች የምታደርገው ሽግግር ያለ አንዳች እንቅፋት መሄድ እንዲችል የመንግሥት ባላስልጣናት ከፊት ለፊታቸው የሚመጣውን ጊዜ እንዴት እንደሚመሩ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ከአሁኑ መወያየት አለባቸው። 

የኮቪድ-19 አመጣጥ ለኢትዮጵያ ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ ፈታኝ በሆነ ሰዓት ነው የሆነው። በዚህ ወቅት ሃገሪቱ የአምስት ዓመታት ፖለቲካዊ ነውጥ ውስጥ ካለፈች በኋላ ነሐሴ ውስጥ ወሳኝ የሆነ ምርጫ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነበረች። ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛቷ ሁለተኛ በሆነችው ሃገር ውስጥ ኮሮና ቫይረስ ያለበት ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ መገኘቱን መንግስት ይፋ ካደረገ ከሁለት ሳምንታት በኋላ መጋቢት 22 ቀን የምርጫ ቦርድ ከማሕበረሰብ ጤና ስጋት የተነሳ ለድምጽ አሰጣጥ የሚደረገው ዝግጅት እንዲቋረጥ አድርጓል። በመቀጠልም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዚያ 2 ቀን የአምስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማጽደቅ በሽታውን እንዲዋጉ ለመንግሥት ባለስልጣናት ሰፋ ያለ ስልጣን ሰጥቷቸዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዚህ ዓመት የሥራ ዘመን በመጭው መስከረም ማለቂያ አካባቢ ከመጠናቀቁ በፊት ምርጫዎች ስለማይደረጉ ጊዜያዊ አስተዳደር ማበጀት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሁን የበሽታውን ስርጭት የማስቆም እንዲሁም ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ሥራ ኑሮዋቸውን የሚገፉ ለችግር ተጋላጭ ሕዝብ ላይ ሊመጣ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና የመቆጣጠር ፈታኝ ሥራ ተጋፍጧል። መንግሥት ለፖለቲካዊ ጭቆና መሳሪያ አድርጎ እስካልተጠቀመበት ድረስ ዋነኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በደፈናው ተቀብለውታል። በተጨማሪም ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የፓርላማው የሥራ ዘመን ከተጠናቀቀ በኋላ ሃገሪቱ የምትመራበትን ጊዜያዊ አስተዳደር ለመቀየስ እነርሱ የምክር ግብዓት እንዲሰጡ ጥያቄ ሊቀርብላቸው እንደሚገባ አመልክተዋል። አብይ ጥሪያቸውን መስማትና ለሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር የረጅም ጊዜ ስጋቶችን ለማስወገድ ሲባል አብሮአቸው መስራት አለበት። 

አዲስ አበባ ለኮቪድ-19 እየሰጠች ያለችው ምላሽ የተዘበራረቀ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት በሽታው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መሆኑን ከገለጸ ከሁለት ቀን በኋላ መጋቢት 4 ቀን ነው ባለስልጣናት በሽታው ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ያደረጉት። ከዚያ ቀን ጀምሮ በምርመራ የተረጋገጡ በሽታው ያለባቸው ሰዎች ቁጥር በፍጥነት ወደ 82 አሻቅቧል፤ ሦስት ሰዎች በዚሁ በሽታ መሞታቸውም ይፋ ተደርጓል። ምርመራ በአቅም ማነስ የተነሳ እስከ አሁን ድረስ ውሱን ሆኖ መቅረቱ አብላጫው ገጠር ነዋሪ በሆነባት 110 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሃገር ውስጥ የሽታው ስርጭት ምን ያህል መሆኑን በትክክል ለማወቅ እንዳይቻል አድርጓል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ የተወሰኑትን ፖሊሲዎችን ባለመከተል የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማስገኘት ሃገሪቱ ከውጭ ለምታስገባቸው እጅግ አስፈላጊ ቁሳቁሶች ግብይት ድጋፍ የሚያደርገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቻይና እና አውሮፓን ጨምሮ መብረር ወደሚችልበት መዳረሻ ሁሉ መብረሩን ቀጥሏል። የፌደራል እና የክልል መንግሥታት ትልልቅ ስብሰባዎችን ማድረግ እና በከተሞች መካከል የሕዝብ መጓጓዝ አገልግሎት መስጠት የተከለከለ መሆኑን ቢያስታውቁም እንኳ ባላስልጣናት ኮቪድ-19ን ለመቆጣጠር ሕዝቡ ሙሉ በሙሉ በቤቱ ተዘግቶ እንዲቀመጥ ትዕዛዝ አላስተላለፉም። የከተማ ሥራ አጥነት መጠን በግምት 20 በመቶ በሆነበትና በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን ወጣት ኢትዮጵያውያን የሰራተኛ ገበያውን በሚቀላቀሉበት በዚህ ወቅት እንደዚህ ዓይነት እርምጃዎችን ለመውሰድ ማመንታት ተንታኞች እንደሚተነብዩት አንድ ሚሊዮን ሰራተኞች ሥራ አጦችን እንዳይቀላቀሉ ለመከላከል የሚደረግ ጥረትን ያሳያል። 

ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ባልተገደበ ሁኔታ እንዲቀጥል መፍቀድ በጥቂት ወራት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በበሽታው እንዲያዙ ሊያደርግ ይችላል።

በሃገሪቱ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ካለው አስቸጋሪ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ተግዳሮቶች አንጻር ኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከባድ ብጥብጥ የማስከተል አቅም አለው። በአንድ በኩል በኮቪድ-19 አማካኝነት ሊመጡ የሚችሉ የማሕበረሰብ ጤና ስጋቶች ሰፊ ናቸው። የሕዝቡ የኑሮ እና የሥራ ሁኔታዎች ለበሽታው ስርጭት በጣም ምቹ ናቸው፤ ምክንያቱም በብዙዎቹ ቤቶች ውስጥ ልጆች፣ ወላጆችና አያቶች በአንድነት በርከት ብለው የቧምቧ ውሃ በሌለበት ነው የሚኖሩት። ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ባልተገደበ ሁኔታ እንዲቀጥል መፍቀድ በጥቂት ወራት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በበሽታው እንዲያዙ ሊያደርግ ከመቻሉም በላይ ሕመሙ የጸናባቸው ሰዎች ብዛት ቀድሞውኑ ደካማ የሆነውና ጥቂት የአየር ማስገቢያ-ማስወጫ እንዲሁም ከ500 በታች የኢንቴሲቭ ኬር ማዕከሎች ያሉት የጤና አገልግሎት ሥርዓት ላይ ከአቅም በላይ የሆነ ጫና ይፈጥርበታል። በ2008/2009 ዓ.ም በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ክሊኒኮች ሁሉ የኦክስጅን ማቅረቢያ መሳሪያዎች ያሏቸው 2 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ነበሩ።     

በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ በሙሉ በቤቱ ተዘግቶ ይቀመጥ ቢባል መደበኛ ባልሆነው የአገልግሎት ሰጭ ዘርፍ ውስጥ የተሰማሩ በዕለታዊ ከእጅ ወደ አፍ ገቢ የሚተዳደሩ ብዙዎችን ጨምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ገቢያቸዉን ያጣሉ። በተጨማሪ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት ከ20 በመቶ በላይ በሆነበት በአሁኑ ወቅት ሁሉም በቤቱ ተዘግቶ ይቀመጥ ቢባል በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን የእህል አቅርቦት አሟጥጦ ሊጨርስ ይችላል። ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የአበባ ላኪ ድርጅቶች የሽያጭ መጠናቸው በቀነሱ ምክንያት አሁን እያሽቆለቆለ ያለው መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሪ እየተሟጠጠ ከሄደ ከውጭ በግብይት የሚገቡ እንደ ነዳጅ ዘይት፣ መድሐኒት እና ማዳበሪያ የመሳሰሉ እጅግ አስፈላጊ ነገሮች እጥረት ሊፈጠር ይችላል። (የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራውን ባያቋርጥም እንኳ ከፍተኛ የንግድ ማሽቆልቆል ገጥሞታል።) ከእነዚህ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አንጻር የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ በሚወሰድ እርምጃ እና በኢኮኖሚያዊ መዘዞቹ ምክንያት ከቫይረሱ የበለጠ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ብለው በሚፈሩት ጠንከር ያለ እርምጃ መካከል የሃገሪቱ መሪዎች መካከለኛ መንገድ መከተል መርጠዋል።

ከሁለቱ መንገዶች አንዱ (ወይም የሁለቱ ጥምረት) ጠንከር ያለ ተቃውሞ ሊያስከትል ይችላል። ቫይረሱ በስፋት ቢሰራጭና ብዙ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦቻቸውን የሚንከባከቡበት አቅም ቢያጡ ብቃት ይጎድላቸዋል ብለው በሚጠረጥሯቸው ባለስልጣናት ላይ በተቃውሞ ሊነሱባቸው ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ሕዝቡ ለራሳቸው እህል ውሃ ማቅረብ እንዳይችሉ የሚያግድ የማሕበረሰብ ጤና እርምጃዎችን ቢወስድ ይህም ከሕዝቡ ተመሳሳይ የቁጣ ምላሽ ሊቀሰቅስ ይችላል። ረብሻ ሊፈጠር የመቻሉ ሁኔታ መንግሥት እጅግ ብዙ ስልጣንን ለራሱ ብቻ እየወሰደ ሳለም እንኳ በዚህ ቀውስ መካከል ሊከተል ለመረጠው ፖለቲካዊ አቅጣጫ ድጋፍ ያገኝ ዘንድ በተለያዩ አካላት መካከል አንድነትን ለማበረታታት ድጋፍ መስጠቱን አስፈላጊ ያደርገዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሰረት በወረርሽኝ በሽታዎች ጊዜ እንዲታወጅ የተፈቀደው አሁን በሃገር አቀፍ ደረጃ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይህንን ቀውስ ለመዋጋት ለፌደራል መንግሥት ያልተገደበ ስልጣን ይሰጠዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚተዳደረው ከዚህ በፊት እንደሚደረገው በሲቪል፣ ወታደራዊ እና በሌሎች የጸጥታ ባለስልጣናት ኮሚቴ ሳይሆን በአብይ ካቢኔ እንደሆነ አንድ የፌደራል ሚኒስትር ለክራይሲስ ግሩፕ ተናግሯል። በመርህ ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በክልሎች የጸጥታ አጠባበቅ ላይ ከሌላው ጊዜ የበለጠ ከፍተኛ የሆነ የፌደራል ቁጥጥርን ይፈቅዳል። ለጊዜው መንግሥት ይህንን ኃይል ለመጠቀም ያስብ እንደሆን ባይታወቅም ይህ ፈቃድ ከሌላው ጊዜ ከፍ ያለ ወታደራዊ እንቅስቃሴንም ይጨምራል።   

የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤቱ በአዋጁ የታወጁ መመሪያዎችንና የተወሰዱ እርምጃዎችን ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ተናሮ ደምቦችን በሚጥሱ ሰዎች ላይ እስከ 200,000 ብር (6,033 ዶላር) ድረስ ቅጣት እንደሚጣልባቸው አስታውቋል። ሆኖም እነዚህ የመንግሥት መመሪያዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ በውል አልታወቀም። በዚያ ላይ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ የበሽታው የስርጭት አቅጣጫ ግልጽ ስላልሆነ አማራጭ ዘዴዎችን ለመጠቀም ክፍት መሆን አስፈላጊ መሆኑን አስምሮበታል። የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤቱ ለመነሻነት የተወሰኑ መመሪያዎችን አስታውቋል፡- ለምሳሌ በአንድ ቦታ ከአራት ሰዎች በላይ መሰብሰብ አይችሉም፤ ሕዝብ ባለባቸው ሥፍራዎች አፍን በጭምብል መሸፈን ግዴታ ነው። ኩባንያዎች የመንግሥትን መመሪያዎች መሰረት ባደረገ መንገድ ካልሆነ በቀር ሰራተኞቻቸውን ማባረር አይችሉም። ለአሁን የበላይ ባለስልጣናት በድሆች ላይ ከሚያስከትለው ከባድ ተጽእኖ የተነሳ በቤት ውስጥ ተዘግቶ የመቀመጥ ትዕዛዝ ለጊዜው እንደማያወጡ አስታውቀዋል። 

ስልጣን ለመጨበጥ እንዲሁም ወደ ፊት ለሚደረጉ ምርጫዎችን ለማሸነፍ የሚጠቅሙ ስልታዊ አድቫንቴጆችን ለማጠናከር ይጠቀምበት እንደሆን የሚል ስጋት አለ።

ብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግሥት አሳሳቢውን የኮቪድ-19ን ችግር መፍታት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዲችል ብለው ፖለቲካን ወደ ጎን ለመተው ዝግጁ መሆናቸውን ቢገልጡም እንኳ በአንዳንዶቻቸው ዘንድ አብይ የአስችኳይ ጊዜ አዋጁን እና የምርጫው ጊዜ መራዘሙን ለራሱ ተጨማሪ ስልጣን ለመጨበጥ እንዲሁም ወደ ፊት ለሚደረጉ ምርጫዎችን ለማሸነፍ የሚጠቅሙ ስልታዊ አድቫንቴጆችን  ለማጠናከር ይጠቀምበት እንደሆን የሚል ስጋት አለ። አንዳንድ የተቃዋሚ መሪዎች በሕገ መንግሥቱ መሰረት ከፓርላማው የሥራ ዘመን መጠናቀቅ ከአንድ ወር ያላነሰ ጊዜ አስቀድሞ ምርጫዎች መደረግ እንዳለባቸው አስታውሰው በዚህ ዓመት ጊዜው ከነሐሴ 30 እንደማያልፍ ገልጸዋል። የምርጫው ጊዜ የተራዘመበት ቀን ከነሐሴ 30 ስለሚያልፍ አስተዳደሩ በሕግ ከተፈቀደለት ጊዜ በላይ ስልጣኑን ለማራዘም እየተዘጋጀ ነው ብለው ይከራከራሉ። ስለዚህ አሁን ያለው መንግሥት የስልጣን ዘመኑ ባለቀ ጊዜ አስተዳደሩን ተቆጣጥሮ የሚይዝ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት መመስረት አለበት ይላሉ።

ቢሆንም ቁልፍ የሆኑ ተዋናዮች ለአብይ ስልታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርግበት ነጻነት ሰጥተውታል። ሁለቱ የኦሮሚያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች (ኦሮሚያ 40 ሚሊዮን ሕዝብ ያሉት በሃገሪቱ በሕዝብ ቁጥር አንደኛ ክልል ነው፤ እንዲሁም ከ2006/2007 እስከ 2010/2011 የረብሻ ማዕከል የሆነ ክልል) ኦሮሞ ነጻ አውጪ ግምባር እና ኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ “በሽታውን ለመዋጋት የሚደረገውን አጠቃላይ ጥረት አናደናቅፍም” ብለው፤ ነገር ግን መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የጤና ቀውሱን ለማረጋጋት ብቻ እንጂ ፖለቲካዊ ነጻነትን ለመገደብ መጠቀም እንደሌለበት ግልጽ አድርገዋል።

አብይ የዚህን ወቅት ችግር የሚፈታበት አፈታት ኢትዮጵያ ለምታልፍበት ነውጠኛ ሽግግር መሳካት ወሳኝ ነው። ኮቪድ-19 ለኢትዮጵያ ፍጥጥ ብሎ የመጣ ስጋት ቢሆንም ለአብይ መንግሥት ይህንን ብሔራዊ የአንድነትና የትብብር ጊዜ ወደ መድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ ሲደርግ የነበረውን ፈተና የበዛበት ጉዞ መልሶ ለማጠናከር እንዲጠቀምበት እድል ይሰጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ በማሕበረሰብ መካከል የሚፈጸሙ ጥቃቶች አሻቅበዋል፤ በቅርቡ ደግሞ ፓርቲዎች ለምርጫ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ውጥረቶች እየጨመሩ በመጡበት በዚህ ጊዜ ፖለቲካዊ አፈና እንደ አዲስ ተጀምሯል። በተጨማሪ በምርጫ ቦርድ በኩል ዝግጅቶች ከተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መዘግየታቸው በሽታው ከመምጣቱም በፊት በሕገ መንግሥቱ ለምርጫው የተቀመጠው የጊዜ ገደብ መዘግየቱ የሚያስከትለው አለመረጋጋት አይቀሬ እንደሚሆን ይታወቅ ነበር። ቦርዱ አሁን የምርጫ ደምቦችን ለማጠናቀቅ እና የምርጫ ጣቢያ ሰራተኞችን ለመመልመል ተጨማሪ ጊዜ ቢያገኝም - መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ወቅት የሚያስተዳድርበት ሁኔታ እና በመሃከል የሚመሰረተው ጊዜያዊ መንግሥት ሊኖረው የሚገባው ቅርጽ ላይ መግባባት እንዲኖር የማድረግ ችሎታው እጅግ በጣም ወሳኝ ይሆናል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት እና ተቃዋሚዎች የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ባይችሉ እና ምርጫውም በመጪዎቹ ወራት በምን መልኩ መደረግ እንዳለበት መግባባት ባይችሉ - አለመቻላቸው ኢትዮጵያን ወደ ሌላ ብጥብጥ ውስጥ ሊያስገባት ይችላል።

የትግልና የተስፋ ወቅት

ያላሰለሰ ሕዝባዊ ተቃውሞ ሃገሪቱን ይመራ የነበረውን ከአራት የክልል ፓርቲዎች የተጣመረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግምባር (ኢህአዴግ) የፖለቲካ ውድድር ሜዳውን ክፍት እንዲያደርግ ካስገደደው በኋላ ሚያዚያ 2010 ዓ.ም በአብይ ወደ ስልጣን መምጣት የብዙ ኢትዮጵያውያን ተስፋ አንሰራርቶ ነበር። ከእርሱ በፊት በስልጣን ላይ በነበረውና በየካቲት 2010 ስልጣኑን በለቀቀው በኃይለማርያም ደሳለኝ ሥራ ላይ በመገንባት አብይ እስረኞችን መፍታት ቀጠለ፤ ደግሞም ከሃገር ተሰድደው የነበሩ ቡድኖችን እንዲሁም ታጣቂ ኃይሎችን ጨምሮ ወደ ሃገር ተመልሰው ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲወዳደሩ ፈቀደ። ከኤርትራ መሪ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋርም ስምምነት አደረጎ በሁለቱ ሃገሮች መካከል ለሃያ ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲቀጥል አደረገ። የኖርዌዩን የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ በተለይ ያስደነቀውና በጥቅምት 2011 የኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲያበረክትለት ያደረገው የዚህ እርቅ መሳካት ነበር። በዚህ ሁሉ ተስፋ መካከል ኢትዮጵያውያንና የሃገሪቱ ዓለም አቀፍ አጋሮች በዚህ ዓመት ለፌደራል እና ለክክላዊ ምክር ቤቶች እንዲሁም ለሁለት ራስ አገዝ ከተማ አስተዳደሮች የታቀዱትን ምርጫዎች አብይ ቃል የገባለት የዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እውን የመሰረት እንደሆን መፈተኛ አድርገው ሲጠባበቁ ነበር።

እርስ በርሳቸው የሚፎካከሩ ክልላዊ እና ጎሳዊ የፖለቲካ አንጃዎች በስልጣን፣ በርዕዮተ ዓለም፣ እና በኢኮኖሚያዊ ግብአቶች ላይ ተጋጭተው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለዋል።

ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ እርስ በእርሱ የተከፋፈለ እና እምነት የታጣበት የአመራር ጥምረት ለሦስተ አስርት ዓመታት ልዩ ልዩ በሆነው እና አልፎ አልፎ በረብሻ የሚታመሰውን ሕዝብ ለመቆጣጠር ይጠቀምበት የነበረው ሥርዓት ከእጁ እየወጣበት ባለበት ጊዜ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጸጥታን ለማስጠበቅ ሲታገል ቆይቷል። እርስ በርሳቸው የሚፎካከሩ ክልላዊ እና ጎሳዊ የፖለቲካ አንጃዎች በስልጣን፣ በርዕዮተ ዓለም፣ እና በኢኮኖሚያዊ ግብአቶች ላይ ተጋጭተው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለዋል፤ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብም አፈናቅለዋል። ሽግግሩን እንደገና ለማጠናከር ባደረገው ጥረት አብይ በ2012 መጀመሪያ አካባቢ ላይ ከኢህአዴግ ፍርስራሽ ውስጥ አዲስ የገዥ ፓርቲ ፈጠረ። የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግምባር (ሕወሐት) ለመቀላቀል እምቢ ቢልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አጋሮቹ የክልሎችን ገዥ ፓርቲዎች ሁሉ በአንድ ድርጅት በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ለማሰባሰብ ችለዋል።

የፈረሰውን የኢህአዴግ ጥምረት ከመተካት በተጨማሪ አብይ ይህንን እርምጃ የወሰደበት ሌላው ዋነኛ ምክንያት ጎሳዊና ክልላዊ ባለ ስልጣናት እርስ በራሳቸው እየተራራቁና እየተገነጣጠሉ ባሉበት ሃገር ውስጥ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ነበር። የክራይሲስ ግሩፕ ባጠናቀረው ዘገባ መሰረት ለምሳሌ በትግራይ እና በአማራ እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሞ መካከል ውጥረቶች እየተባባሱ ነበር። በተግባር ሲታይ ግን አንዳንድ ክልላዊ እና ተቃዋሚ መሪዎች የአብይ የመጨረሻ እቅዱ ክልላቸው በብዙ ትግል ያረጋገጠውን ራስን በራስ የማስተዳደር ነጻነት ለመንጠቅ እንዳይሆን ከመፍራታቸው ጋር ተያይዞ የክልላዊ ገዥ ፓርቲዎች መፍረስ ጎሳዊ የብሔር ግጭቶችን እሳት ለማራገብ መንስኤ ሆኗል።

የኢህአዴግ መስራች እና የረጅም ጊዜ አንጋፋ መሪ የሆነው ሕወሐት በተለይ ጠንከር ያለ ቅሬታ ተሰምቶታል፤ አዲሱን ፓርቲ ለመቀላቀል እምቢ ለማለቱ በብልጽግና ፓርቲ ስር ለመጠቃለል ፈቃደኛ ከሆኑት ሌሎች የኢህአዴግ ፓርቲዎች ጋር ያለውን የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶችን እና ውጥረቶችን እንደ ምክንያት አድርጎ አቅርቧል። በቀጣይነትም አብይ ቀሪዎቹን የሕወሐት ተወካዮች ከካቢኔው አሰናብቷቸዋል፤ የትግራይ ክልልም ከቀረው ፌረዴሽን ያለው ርቀት ከዚያ ጊዜ አንስቶ እየሰፋ ሄዷል። የትግራይ ወጣት አክቲቪስቶች ከፌደሬሽኑ የመገንጠል ሃሳብን እያራገቡ ባሉበት በአሁኑ ሰዓት የትግራይ መሪዎች የክልሉን የደሕንነት ኃይልሎች ማጠናከርና ፌደራላዊ መንግሥቱን መተቸት ቀጥለዋል።

የማዕከላዊ መንግሥቱ ችግሮች ከትግራይም የሚያልፉ ናቸው። በዚህ ዓመት መንግሥት በሕገ መንግሥቱ መሰረት ለምርጫ በተወሰነው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫ ከመደረጉ በፊት ለፍትሃዊ ምርጫዎች የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን አመቻቻለሁ ብሎ ቃል ከገባ በኋላ ሳያመቻች በመቅረቱ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የትችት ዱላ ተሰንዝሮበታል። በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት በፊት የነበሩ አምባ ገነን መንግሥታት ይጠቀሙዋቸው የነበሩ እንደ አክቲቪስቶችን ማሰር እና ማናገላታት እንዲሁም የስብሰባ እና የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃዶችን መከልከል የመሳሰሉ ስልቶችን እየተጠቀመ ነው ብለው ከኢትዮጵያ ዙሪያ ልዩ ልዩ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መሪዎች ቅሬታ አቅርበዋል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተጨማሪ ልክ የገዥው ጥምረት በ2010 እና በ2015 ለተቀዳጃቸው ድሎች ዝግጅት እንዲረዳው እንደተጠቀመው ሁሉ የብልጽግና ፓርቲው የመንግሥት ሃብቶችን በተደጋጋሚ የራሱን ዓላማዎች ለማሳካት ተጠቅሞባቸዋል ሲሉ ቅሬታ ያቀርባሉ። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት ጠንከር ያለ ትግል ውስጥ ካሉት ተቃዋሚዎች መካከል አንዳንዶቹ በበይፋ ባይሆንም የምርጫ ውድድር ሜዳው አሁንም ለገዥው ፓርቲ እንዲያግዝ ተደርጎ ያጋደለ ከሆነ ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች ሊደረጉ እንደሚችሉ እየተናገሩ ነበር።

አበረታች ምልክቶችና የተጋረጡ ተግዳሮቶች

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአብይ መንግሥት የጊዜውን የጤና ስጋት ለማቃለልም ሆነ ምርጫዎቹ በሚደረጉበት ወቅት የሃገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ እንዲቻል መጪውን የሽግግር መንግሥት ቅርጽ ለማስያዝ ሁሉን ያካተተ፣ ከሁሉም ምክርን የሚያደምጥ አሰራርን መከተሉ አስፈላጊ ነው። መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ስጋትን ለመቆጣጠር ከተቃዋሚዎች ጋር ተባብሮ የመስራት ፍላጎት እንዳለው የሚጠቁሙ አበረታች ምልክቶች ታይተዋል። በሚያዚያ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ውስጥ የአብይ ካቢኔ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከማወጁ በፊት አብይ ለኮቪድ-19 የሚሰጠውን ምላሽ ለመወያየት የፓርቲ መሪዎችን በቢሮው ውስጥ ሰብስቦ ነበር።

የአብይ መንግሥት የጊዜውን የጤና ስጋት ለማቃለልም ሆነ ምርጫዎቹ በሚደረጉበት ወቅት የሃገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ እንዲቻል መጪውን የሽግግር መንግሥት ቅርጽ ለማስያዝ ሁሉን ያካተተ፣ ከሁሉም ምክርን የሚያደምጥ አሰራርን መከተሉ አስፈላጊ ነው።

ይበልጥ አሳሳቢ የሚሆነው ጥያቄ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ሕጋዊ የስልጣን ዘመኑ ካበቃ በኋላ ባሉት ቀናት ውስጥ ሕጋዊ በሆነ መንገድ መምራቱን ለመቀጠል ምን አይነት ዝግጅቶች እንደሚያደርግ ነው። ይህ የሚሆንበት ቀን ገና በውል አልታወቀም። ከላይ እንደተገለጸው መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም ሊሆን ይችላል፤ ግን ካቢኔው እና ፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ቢያራዝሙ አብይ ሕጋዊ የስልጣን ዘመኑ ከዚያ ቀን ያልፋል ብሎ ሊከራከር ይችላል። ይህ ክርክር ተገቢ ይሁንም አይሁንም አንዳንድ የተቃዋሚ አንጃዎች በዚያ ወቅት ውስጥ የአብይ መንግሥት ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ፤ ከዚያም ሊከተል የሚችለው ግጭት የረብሻ መንስኤ ሊሆን ይችላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች አብይ ፓርላማውን ለመዝጋት የሚያስችለው ሕገ መንግስታዊ አንቀጽ በፓርላማው ፈቃድ ለመጠቀም ሊያስብ ይችላል ይላሉ። ይህን ቢያደርግ እርሱ እና ፓርቲው ብሔራዊ ምርጫዎች እስኪደረጉ ድረስ ለስድስት ወራት ያህል የባላደራ አስተዳደር መመስረት ይችላሉ። ግን ይህ አደራረግ በሕጉ የተፈቀደ ቢሆንም የሚፈጥራቸው ችግሮች አሉ። የምርጫ ቦርዱ ታሕሳስ 19 ቀን 2013 እና የካቲት 21 ቀን 2013ን የምርጫ ቀኖች አድርጎ ቢያቅድም ውሳኔ አላደረገም፤ በሌላ በኩል ደግሞ የስድስት ወራት ጊዜ ኮቪድ-19ን ፈጽሞ ለመቆጣጠር እና ለምርጫ ዝግጅቶችን ለማድረግ በቂ ጊዜ ላይሆን ይችላል። በተጨማሪ የባላደራ መንግሥት የኮሮና በሽታ ውጤቶችን ሁሉ ለመቆጣጠር የሚያስፈልግ ሕጋዊ ስልጣን ላይኖረውም ይችላል።

ለአብይም ሆነ ለተቃዋሚዎች የሚያዋጣው መንገድ በየራሳቸው አቋም መካከል ያሉትን ልዩነቶች የማያጠፋ ፖለቲካዊ ስምምነት ማዘጋጀት ነው። ለአብይ አንዱ አማራጭ ጊዜያዊ መንግሥት ለመመስረት ከተቃዋሚ መሪዎች ጋር መሥራት ሲሆን በዚህ ውስጥ ለተቃዋሚዎች የአማካሪነት ድርሻ መስጠት ይጠበቅበታል። ኮቪድ-19ን ለመዋጋት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከዛኔ ድረስ ባይጠናቀቅም የፓርላማ የሥራ ዘመን ከተጠናቀቀ በኋላ ይህ አይነቱ አሰራር ወዲያው ሊቀጥል ይችላል። በዚህ አሰራር መንገድ የተቃዋሚ መሪዎች ወደ አብይ ካቢኔ ውስጥ እንዲገቡ ባይጋበዙም እንኳ መንግሥት ለማንኛውም ከምርጫ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ከተቃዋሚዎች ኮሚቴ ጋር ተመመካክሮ ወደ ጋራ ውሳኔ እንዲመጣ ሊጠየቅ ይችላል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የፌደራል እና የክልል ጸጥታ ኃይሎች እንዴት አብረው እንደሚሰሩና እንደሚግባቡ የሚገልጽ ስምምነት ከሌለ በትግራይ እና በማዕከላዊው መንግሥት መካከል ያለው ግጭት ያልታሰቡ መረጋጋትን ሊያጠፉ የሚችሉ መዘዞችን ሊያመጣ ይችላል።

ለዚህ ዓይነቱ ጊዜያዊ ሥርዓት መሰረት ለመጣል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋነኞቹ የፖለቲካ ተዋናዮች መካከል ብሔራዊ ምክክር እንዲደረግ መጠየቅ አለበት፤ ይህም ከማሕበረሰብ ጤና ቀውሱ አንጻር በጽሑፍ አቋም መለዋወጥንና በርቀት ውይይቶችን ማድረግ ያካትታል። ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ውይይቶች ትኩረት ማድረግ ያለባቸው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በስተጀርባ ያለውን የጋራ ስምምነት ማጠናከር ላይ እና የፓርላማ የሥራ ዘመን እንዲጠናቀቅ ከታቀደለት መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ ያለውን የጊዜያዊ አስተዳደር ጊዜ እንዴት ባለ አያያዝ መምራት እንደሚገባው ነው። ከእነዚህ ውይይቶች ጎን ለጎን ወይም በተናጠል በሚደረግ ውይይት የፌደራል ባለስልጣናት ከትግራይ መሪዎች ጋር የፌደራል አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መጋቢት 17 ቀን በክልሉ ከታወጀው አዋጅ ጋር እንዴት እንደሚቀናጁ መነጋገር አለባቸው። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የፌደራል እና የክልል ጸጥታ ኃይሎች እንዴት አብረው እንደሚሰሩና እንደሚግባቡ የሚገልጽ ስምምነት ከሌለ በትግራይ እና በማዕከላዊው መንግሥት መካከል ያለው ግጭት ያልታሰቡ መረጋጋትን ሊያጠፉ የሚችሉ መዘዞችን ሊያመጣ ይችላል። የአብይ የጸጥታ ኃይሎች ቅድሚያ ስምምነት ሳይደረግ በትግራይ ውስጥ ያላቸውን ቁጥርም ሆነ ሚና ለመጨመር የሚያደርጉት ማንኛውም ሙከራ ከክልላዊ መሪዎች ጠንከር ያለ ተቃውሞ ሊገጥመው ይችላል።

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እና ከሽግግር ጊዜው ጋር የተዛመዱ ቁልፍ ጉዳዮች ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ፓርቲዎቹ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር የሚመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር እድሉን መጠቀም አለባቸው። ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል። ለምርጫ ዝግጅቶች በሚቀየሰው መንገድ ውስጥ ለፍትሃዊ ምርጫ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር ጋር እና ተቃዋሚዎች በምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻዎች ውስጥ ከሚገጥማቸው ገደቦች ጋር በተያያዘ የተቃዋሚዎችን ቅሬታ በምን መልኩ ማስተናገድ እንደሚያስፈልግ ውይይቶች የጋራ ዓላማዎችን ለመቅረጽ መዘጋጀት አለባቸው። በውይይታቸው ወቅት ሊነሱ የሚችሉ ሌሎች ሰፋ ያሉ ርዕሰ ጉዳዮች ፖለቲካዊ የፉክክር መድረኩ ሳይዘጋ እንዴት ተደርጎ ሕግና ሥርዓት በተዋጣለት መንገድ ሊከበር እንደሚችል፤ ሕገ መንግሥቱ ላይ ለውጥ ለማድረግ የሚቀርቡ ጥያቄዎች፤ በአማራ እና በኦሮሞ፣ በአማራ እና በትግራይ መካከል ያሉ የግጭት ስጋቶችን ማረጋጋት፤ አዲስ አበባን ማን ያስተዳድራት የሚለው ክርክር፤ እና የደቡብ ብሔሮች ራስን የማስተዳደር ጥያቄዎች  ይጨምራሉ።

የውጭ አጋሮች ኢትዮጵያ እነዚህን ተግዳሮቶች መፍታት እንድትችል መርዳት ይችላሉ። የዓለም ባንክ 83 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የዓይነት አስቸኳይ ድጋፍ በማድረግ እንደጀመረው መንግሥት የኮሮናን ስርጭት ለመቆጣጠር ለሚያደርገው ጥረት ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ እነዚህ አጋሮች መጪውን ወቅት መንግሥት ለብቻው የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ለመቀነስ እና ለፍትሓዊ ምርጫዎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያግዙ ተጨማሪ ሥራዎችን ለመስራት መጠቀም አለባቸው። እርዳታ ሰጭዎች ማንኛውም ፓርቲ (አብይን ጨምሮ) በደፈናው ድጋፋቸውን ማግኘት እንደሚችል ከመናገር መቆጠብ አለባቸው። በዚያ ፈንታ ዋነኛ ዓላማቸው ኢትዮጵያ ወደ መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ለምታደርገው ሽግግር ጠንካራ መሰረት መጣል የሚችለውን ትክክለኛ የምርጫ ሂደት መደገፍ መሆኑን ሊያሰምሩበት ይገባል።

ማጠቃለያ

የኮቪድ-19 በሽታ እስከ አሁን ድረስ በዓለም ዙርያ ከፍተኛ ሞት እና ጉዳት አስከትሏል። እስካሁን ካደረሰው ጉዳት ሁሉ የከፋ ጉዳት ገና ወደፊት ሊመጣ ይችላል። ከኢትዮጵያ ተጋላጭነት አንጻር ደግሞ በሽታው በሕዝቦቿ መካከል በስፋት ቢሰራጭ ሃገሪቱ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ሊገጥማት ይችላል። ግን ደግሞ ቀውሱ አንዳንድ መልካም አጋጣሚዎችንም ፈጥሯል። ወረርሽኙ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ጉልህ ለውጥ በማምጣት ወደ ከፍተኛ ደም መፋሰስ ሊያመራ የነበረውን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን ለማራዘም በቂ ምክንያት እንዲኖር አድርጓል። በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በአንድ ላይ እንዲሰባሰቡ ውዴታም ምክንያትም ሆኗቸዋል። አሁን የመጣውን የጤና ቀውስ አብረው ለመጋፈጥ በትብብር መስራት አለባቸው፤ ከዚያም በተጨማሪ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ በመካከል በሚመጣው ጊዜያዊ አመራር ወቅት አገሪቱን ለማስተዳደር ሰፋ ያለ ድጋፍ ያለው እቅድ ማዘጋጀት አለባቸው። ከዚያ በኋላ ይህንኑ የትብብር መንፈስ የሃገሪቱን ሽግግር ያስተጓጎሉ ጉዳዮችን ለመፍታት መጠቀም አለባቸው።   

Subscribe to Crisis Group’s Email Updates

Receive the best source of conflict analysis right in your inbox.